ያን የዘመን ጉዲፈቻችሁን፤
ይደፈረስ ዐይናችሁን
ያቀጠነ ድምፃችሁን
እባካችሁ፤ አላምዱኝ ፍርሃታችሁን።

ያን ቀን ኦቶቡሱ ላይ
ስትሣፈሩ የሆነውን ሳይ
ከአንቀልባው እንደ ሾለከ ጨቅላ
ነብሴ ጮኸች ከሾህ ተንጋላ።
ደማቅ ሰማያዊ ቦግ ታጥቀህ
ጭስ መሳይ እጅ ጠባብ ለቅህ
ኮት ብለህ ዕድፍ ደርበህ፤
በግራ እጅህ ከዘራህን
በቀኝህ የልጆችህን እናት ጨብጠህ፤
ገባ ስትል “ወንድምዮ” የሌላው ዐይንኮ ገላመጠህ!
ኮስታራ ገጹ ገረመመህ፣
በሹክሹክታው አገለለህ
ባንድ አድሞ አንተን ለየህ፣
አትጠጋን አትቅረበን አለህ!

ከፊቷ አንገቷ ጠቁሮ፣ ደረቷ ጠቁሮ
እግሯ በንቃቃት ተቦርቡሮ፣ ተሸርሽሮ
ቦብሊን ሸንሽና ለብሳ
በላዩ ዶቃ ነገር፣ ጨሌ አፍሳ
ጸጉሯን በቅቤ አርሳ
ጮጮዋን እንደ ጨበጠች፣ የት ትቀመጥ፣ የት ታኖርት?

እንደ ላስቲክ እየሰፋ ቦታውን አጠበቡባት።
በልብሷ ተጠየፏት።
በጠረኗ ተሰቀቛት።

እስቲ በል፣ ይህችን እናት
የሀገር እናት የት ታኖራት?

ካርኒ ቆራጩ የተግባር ቃሉን ነፍጓችሁ
ቀና ድምፁን ደብቋችሁ
ኋላ ወስዶ፣ ከዕቃ ጋር ሲወሽቃችሁ፣
ዐልፎ ከእድፋም ልብሳችሁ።

ግን የኔ እንባ፣ አልጠፋኝም እንደሆነ የይስሙላ
የንፉግ ምጽዋት ዘለላ።
ወይ የቅንጦት ወለላ።
እናንተ እንጂ፣ እናንተ እንጂ ወዛችሁን ያነባችሁ
እናንተ እንጂ፣ እናንተ እንጂ ሰቀቀን የቻላችሁ
….ዳፈን፣ ለታሪክ ዋስትና የከፍላችሁ።

1968 (ለታሪክ ፈለግ ጧፍ ለሆኑ ወገኖቼ)

ከየብርሃን ፍቅር መጽሃር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *