ፃእዳ ሳርያን ለብስው
በሓምራዊ ኩታ ኣምረው
ካባ ደርበው
ኣርዝመው ጢማቸው 
ከበራፍህ ቆመው
መቋምያም ይዘው
ሲያምር ወዛቸው።

ሲዘርፉ በቴለቪዥን
በፈገግታ በጥዑመ ልሳን
እባብ – እርግብ
ተኩላ – በግ
ደረቁን – እርጥብ
ክፉውን – ደግ
ሲያረጉ ፅንሰ-ሃሳብ።

ሰኞ – ከቤት ተወጥቶ
ማክስኞ – ሮብ – ሓሰት ተዋሽቶ 
ሓሙስ – ተበልቶ – ተጠጥቶ
ዓርብ – ገርፎ – ገድሎ
ቅዳሜ – ለብቻ ገለል ብሎ
ሰንበት – ተፀፅቶ – አልቅሶ!

እግዚኦ ይቅር በለን
ከቡዙሓን አትጨምረን
ፍትህ ካለ  ??? – አታሳጣን
በጠባቧ በር ኣስገባን
በቀጭኗ መንገድ ምራን።

ፍረድ እንደ-ገፃቸው
ኣትመልከት ሞያቸው
የሚኖሩት ለእንጀራቸው
ስልጣን የጠማቸው
ኣስማት ያማራቸው!!!

እግርን ያጠብከው?
ትሕትና  ልታሳየው
ፍቅርን እንድታስተምረው
ለዚሁ ከሆነ የፈጠርከው
ከጅምሩ በተውከው።

ለሱ  ምልክት ይበቃዋል
ኮከብ-ጨረቃ-መስቀል
መንጋ ከመንጋ ይለያያል
አንዱን አንዱን ይወነጅላል።

ግን –  ድክመት –  ያዳም ይሆን?
            ብልሃት – የሂዋን
              ቅናት – የቃኤል
            ቸርነት – የኣቤል!!!

      አቤል’ማ ድንግል ኣበባ
     የዋህነቱን ይዞ መቃብር ገባ
    ፍሬ ኣልባ  እንዳናገኘው
     በገነት ቃኤል ቀጠፈው።

በዚያን ዘመን ፀሓይ ጠለቀች
ነጸብራቅዋ ጨረቃ ቀረች
ኮነ – ሆነ – ዉዳሴ ከንቱ
እብነ ኣድማስ  ዘእይትወቀር ወእቱ።

10/09/2017 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *