ከውጭ፣ ከውርጭ ቤት ሲገቡ
ሙቅቱ፣ ስሜቱ
እንዴት ነው ቢሉሽ – ትርንጎውን
ትንፋሽሽ በሮማን ከንፈርሽ –
እፍፍፍ… በዪባቸው
ኣትፍሪ፣ ኣትፈርያቸው

 “እንዲህነዋ!”        በያቸው።

የዓጋሙ፣ የቀጋው፣ የኣደሱ፣ የጥሪኝ
መዓዛው፣ ሽታው
እንዴት ነው ቢሉሽ – ጋሜሽን
ግለጭው፣ ሽሩባሽን ፍቺው…
ኣሳዪኣቸው…
ኣትፍሪ፣ ኣትፈርያቸው
“እንዲህነዋ!”      በያቸው።

ጨረቃ ብቅ ስትል ከዳመና ውስጥ
ብርሃንዋ፣ ድምቀትዋ
እንዴት ነው ቢሉሽ – መቀነትሽን
ፍቺው፣ ኣውልቂው ልብስሽን…
ኣሳዪኣቸው…
ኣትፍሪ፣ ኣትፈርያቸው
“እንዲህነዋ!”        በያቸው።

የሱስሙ ታንን ያስነሳው
በረቂቁ ታምር
እንዴት ነው ቢሉሽ – ጠጋ በዪኝና
ከንፈሬ ላይ ሳሚኝ – ፍቅርሽን
ኣሳዪኣቸው…
ኣትፍሪ፣ ኣትፈርያቸው
“እንዲህ ነዋ!” በያቸው።

             እንዲህ… እንዲህ… እንዲህ…

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *