አስምአኒ ነገረ ፅድቅ
ዘያስተፈስህ ህሊና
አስምአኒ ከጌታ ሰማኒ
ዕዝነ ልቡናዬን ክፈትልኝ
ዓይነ ህሊናዬን አብራልኝ
የጠጠረው እንዲላላ … ውስብስቡ እንዲገራልኝ

    አስምአኒ…
ከጌታ ሰማኒ…
ህያዊት ልባዊት … ነባቢት ነፍሴ ጋር አስታርቀኝ
እኔም ጠፍቼ እንዳልባክን
አንተም እንዳትርቀኝ
ዝንጉ ነኝ እረሳለሁ … ስባዝን የሚመሽብኝ
እስኪነጋም ትዕግስት የለኝ …
ዕንቅልፍ አልባ ነኝ
እንዳልል
ሌት የሚቀሰቅስ
ያሳብ መስተንግዶ አለብኝ
አጥግበኝ ከፍቅርህ ድግስ
አስበኝ በመንግስትህ
ለከፈልክልኝ ሁሉ … ሌላንኳ መድረግ  ባልችል
ምስጋን እንድልሰስትህ

አስምአኒ…
ከጌታ ሰማኒ …
ፈቃድህ ይምራት ቃሌን … ላንተ ሰጠሁ አንደበቴን…
በፈተና ወድቄ እንዳልቀር አፅናልኝ ዕምላት ጉልበቴን
ትዕዛዝን ጠብቄ ለትንሳዔ ክብር እንድበቃ
አንተ ብቻ ነህ ያለኸኝ የኔ የምለው ጠበቃ

አስምአኒ…
ከጌታ ሰማኒ…
አስምአኒ ነገር ፅድቅ ዘያስተፈስህ ህሊና
ወያስዝብ ልቦና
አንተ ብቻ በውስጤ ከብረህ
ስላንተ ብቻ እንድመሰክር
ላክልኝ ጰራቅሊጦስን
በመንፈስ ቅዱስ እንድሰክር
አጥግበኝ ከወይን ጠጅህ
ለሥጋ ወደሙ ማዕረግ አብቃኝ
ካሸለብኩበት ቀስቅሰህ አንቃኝ

አስምአኒ
በአክናፍህ አቅፈህ ደግፈህ
አውጣኝ ከባብሎን እሳት
ተማርኬ እጄን እንዳልሰጥ ያይኔ አዋጅ እንዳያስተኝ
እባክህ ነፍሴን አስታውሳት
በወረት ተደልዬ በውዳሴ ከንቱ እንዳልረክስ
ሁለት ዛፍ ልውጣ ብዬ ተፈልቅቄ እንዳልረከስ
የሥርዓትህን መንገድ እስተምረኝ
እኔ’ንኳ ሌላ ሌላው ሌላው ቢይምረኝ
ፃም ፀሎት ስግደትን ብቻ አጣፍጥልኝ
ፍታልኝ እንቆቅልሹን እንካ ስላንቲያ አታስወድደኝ
መከራ እንደደራሽ ውሃ በጠራራ ጣይ እንዳይወስደኝ
እንደመልከ ፃድቅ ካህን
ጠርተህ መርጠህ ባርከህ
ቀብተህ እንደቀደስከው
ይኽን አጉራ ዘለል ልቤን ገርተህ
ቃለህትወትን ስበከው

ምንጊዜም ካንተ ብቻ ነው ተስፋ
ምንጊዜም ካንተ ብቻ ነው ድህነት
ማንም እንዳንተ የለው
ሰፍ ተፍ ቢል ስለቱ የሆነለት እየመሰለው
የሰማታትን ክብር አስረዳኝ
በመላዕክት ዝማሬ አጅበህ
ጠግንልኝ የነፍሴን ስብራት
አሳም ሞልቶላት ትሳቅ
ምሉዕ በኩሊሄ ነሽ ብለህ
ምህረትህን አብስራት
እግረ ሙቅ ተኮድኩዳ በደረታ ክምትድህ
በይቅርታ ዓይንህ እይልኝ
መቸም አንተን አይገድህ
ሰምዓኒ
ከጌታ ሰማኒ
መንግስትህ በሰማይ እንደሆነች
እንዲሁም በምድር ትሁን
አሁን!

መንበረ ማርቆስ
ታኅሳስ / 95

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *