መቁጠሩንስ ቆጥራል የትግል አቡጊዳ
በደሙ እየጻፈ በሕይወት ሠሌዳ
ላያሌ ዓመታት ለረዥም ዘመናት
ጨሶ እንደ ርጥብ እንጨት ተቃጥሎ እንደ እሳት
እንደ ወዙ ልቡን ስይገብር ለጠላት።
መቁጠሩንስ ቆጥራል፣ …
ቸል ብሏት አያውቅም
የሕይወትን ፊደል ዳር ሁኖ ዳር ቆሞ
ቃል ኪዳን ነበረው በራሱ ጉባኤ ምሎ ተፈጥሞ
የራሱ ሊያደርጋት ወድቆና ተነስቶ ሮጦና አዝግሞ።
ቃልኪዳን ነበረው፣
የሕይወትን ፊደል ቅንጣትና ዘራን
እጅግ ለምለም ቡጧን
ወይ ዕውቀት ፍሬዋን፤
በመንቆር ጣቶቹ ሰቅዞና አፍኖ
የያዛትን ምስጡን ትሉን ትላትሉን
ከላይዋ አርግፎ አብኖ አትኖ
በወዙ ሊያፋፋት
በአምሳሉ ሊቀርፃት እንዲኖራት መቅኖ፤
እንዲኖራት ጤና ሰላም ብልጽግና
‘ማይታጠፍ ሰንደቅ ከቶ እማይገሥ አርማ
                             የእምነት ዕፁብ ፋና።
እኖሆም አልቀረ፣
ቃል ከዳን ቃል ሁኖ አየነው ሲለማ
ከጨለማ ልጆች ከምስጣምስጥ ትሎች ብርሃንን ሲቀማ
ለትግሉም መዘክር ለድሉ ዋስትና
ለዛች የሕይወት ፊደል
ለዛች የፊደል ዘር
ለዛች የዕውቀት ፍሬ ሐውልት ቀረፀና
እውነትን ውበትን ፍቅርን አርነትን በላይዋ ነደፈ
በስሙም ሠየማት፣
በብሩህ ደም-ቀለም “ሠርቶ አደር” ሲል ጻፈ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *