(የአንድ ኢትዮጵያዊ ራዕይ)

ሃበሻነት ምንድን ነው ብዬ ራሴን ስጠይቅ…
ሆደ ባሻነት ነው አለኝ ውስጤ።
ሃበሻስ ማን አልኩ
          ደሞ …እሱማ ባሻህ
         ባሰኘህ ባስመለከተህ …
         እስከደከመህ … እስከታከተህ …
የሚል ቃል ሰማሁ…
እ … ብዮ ከገባሁበት ያሳብ ሰመመን …
ቃል የሚለው ድምፅ አነቀኝ … አነቃኝ …
አንቀራጨሁት
         ብሎም እንደምርቅ አነቀኝ … አስጨነቀኝ
እንደበካር ምጥ ተንበርክኬ
          እስክፈለቀቅ ድረስ አስጨነቀኝ …
                   የናቴን … የህቴን … የሚስቴን
          ወልዶ ማሳደግ ሚስጢር … ያባትን …
          የወንድምን … የልብን እንቆቅልሽ …
          የዕድሜን ምን አውቅልሽ
ሳትፈታ
          መንገድ አትግባ ብሎ አበክሮ አስጠነቀቀኝ …
ሃበሻ … ሃበሻ … ሃበሻ ቃሉ ውስጥ ተመላለስኩ
አወጣሁ አወረድኩ … አስተነተንኩ … ክለስኩ …
ሃበሻ … እንዳሰኘህ እንደመሻህ …
ሆደ ባሻነትን ሃበሻ ይንገርህ…
ለመሆኑ ማነኝ እኔ ብዮ ነፍሴ ጋር ተፋጠጥኩ …
         ማነኝ እኔ … ምንድን ነኝ …
የሌላው አስቆጥቶ … የራሴ የሚያደነድነኝ …
አዝኜ የሰጠሁትን አለመቁጠሬ …
          ባልበላሁት የሚያሳድነኝ …
ምንድን ነኝ …
ቀጠልኩ …
         በአዕሞሮዬ ውስጥ ችሎት ተሰየመ …
አንቀጽ የሌለው ብይን ሊሰጥ ተወሰነ …
          ከሳሽ በግራ ተከሳሽ በቀኝ ቆመ …
ዳኛውም ቦታቸውን ያዙ … የሚገርመው ግን
          ሦስቱም ቦታ ያለሁት እኔ ነኝ …
ተጀመረ …
         ስምህን ተናገር ተባልኩ …
መልሼ ራሴን ለራሴ ማስተዋውቁ አሳፈረኝና
          ላፍታ … ፀጥ አልኩ …
          ማነው ስምህ …
          ዝም …
ስምህን አታውቅም …
ሰርቆ እንደተያዘ ቀጣፊ እየተርበተበትኩ
          «           » አልኩ …
          ታውቀዋለህ …
          ማንን …
          ተሳከረብኝ …
          «ቃል» …
ለካ ቃልም ይጨንቃል …
ለካ ቃልም ያልቃል …
ለካ … ቃልም እያልኩ ባስብ ማዕበል
እየቀዘፍኩ መነሻዬን ረስቼ …
መድረሻዬን ትቼ
እንደአየሩ ፀባይ የሞት ሞቴን ተፈራግጨ …
ልቤን ገዛሁ …
ተመስጌን ብዬ በረጅሙ ተነፈስሁ …
ሌላ የብርሃን ፀዳል ፍንትው ብሎ ፊት ለፊቴ በራ …
ልብን መግዛት … ሃበሻነት ምንድን ነው …?
ልብን መግዛት … ሃበሻስ ማን … ልቡን የገዛ…
           ዋልያ ገብስ እያበላ የሚያሳድግ …
ለባለጌ ጥቁር እንግዳ ባጭር ታጥቆ የሚያደገድግ
ሆዱ አገር አንጀቱ ድርብ ድግ …
ሃበሻ … ልቡን የገዛ …
ሲማር … በሰው ፊት እሳት …
ሲቆርጥ … ባገሩ … በነገሩ … በዘገሩ…
ብሎም በማገሩ …
ሆኖ ሲገኝ ጊዜ ጉዳዩ … ሙዳዩን ማየት
           ጛጉቼ ስከፍተው … ላይኔ ያው ኩሌ …
ለልክፍቴ … ያው ጨሌ …
በቃ … ሌላስ …?
          ሌላ ምን ያምርሃል …
                    ላይኔ … ያው ኩሌ
ለልክፍቴ ያው ጨሌ
ብቻ …
          ቅምብቻ ካለህ … ማጀትህ ውስጥ ስልቻህን
          ቂም ካለህ … ጭነትህ ውስጥ ቅምጣናህን
          አልስማም ካልክ …
         ጆሮ ገድፍ በጣም ጠንቶብህ
         ደሞ … አልበቃህ ብሎ …
                    በሞትኩት ካልክ …
          ፀፀትህን በሞረድ እየሳልክ …
ቅዥት መሰለኝ
የተንሳሁበት ሃሳብ … ውሉ እንደጠፋ ፈትል
         ልቃቂውን መዘርገፍ ቃጣኝ …
ሃበሻነት ምንድን ነው … ልብን መግዛት …
ሃበሻ ማነው … ልቡን የገዛ …
እንግዲህ ልቡን ሳይገዙ ሃበሻን
ማነው ምንድን ነው ማለት ያባት ቢሆንም
እንዳወዳደቁ ይጠባል ተብሎ …
ሃሳቡን ሳልከተል ደንግጨ ተመለስኩ …

ለሃበሻ ምስታወሻ
ሥላሴ-ህዳር/1995 ዓ.ም.
ከመናገሻ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *